Awi Zone Environmental Protection
Creating awareness around environmental protection and its benefits over community
25/09/2026
መስከረም 15/2019 ዓ.ም
እንኳን ለ2019 ዓ.ም የደመራና የመስቀል በዓል በሰላም አደረሳችሁ
በመጀመሪያ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለ2019 ዓ.ም የደመራና የመስቀል በዓል እንኳን በሰላም፣ በጤናና በፍቅር አደረሳችሁ እላለሁ!
የመስቀል በዓል የእውነተኛ ፍለጋ፣ የደስታ፣ የመተሳሰብ፣ የይቅርታና የአንድነት መገለጫ የሆነ ታላቅ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ቅርሳችን ነው። የደመራው እሳትና ጭስ ጨለማን አግልሎ ብርሃንን እንደሚገልጥ ሁሉ፣ ይህ በዓል ለአገራችንና ለዞናችን ሰላምን፣ እድገትንና አዲስ ተስፋን ይዞልን እንደሚመጣ ሙሉ እምነቴ ነው።
የመስቀል በዓል በተፈጥሮ ውበትና በለመለመ አካባቢ መካከል የሚከበር በዓል እንደመሆኑ መጠን፣ የተሰጠንን የተፈጥሮ ጸጋ መጠበቅና መንከባከብ የሁላችንም ተቋማዊና ዜጋዊ ኃላፊነት ነው። በበዓሉ ወቅት የደመራ ዝግጅቶችን ስናደርግም ሆነ የበዓል አከባበራችንን ስናከናውን፦
• አካባቢያችንን ከማንኛውም ዓይነት ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ በማጽዳት፣
• አከባቢንና ወንዞችን ከብክለት በመጠበቅ፣
• ጽዱ፣ አረንጓዴና ለኑሮ ተስማሚ የሆነ አካባቢን በመፍጠር በዓሉን በደስታ እንድናከብር ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
በድጋሚ በዓሉ የሰላም፣ የጤና፣ የፍቅርና የስኬት እንዲሆንልዎ እመኛለሁ!
መልካም የደመራና የመስቀል በዓል!
ወ/ሮ ብዙነሽ ይሁኔ
የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ
24/09/2026
ድንቅ ተፈጥሮ
23/09/2026
የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመግታት ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት።
20/09/2026
መስከረም 10/2019 ዓም
የመስቀል በዓል አከባበር እና የደን ጥበቃ መልዕክት
መግቢያ
የመስቀል በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (UNESCO) በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ የዓለም ቅርስ ነው። ይህ በዓል በሀገራችን በሁሉም አካባቢዎች የሚከበር ሲሆን፣ አከባበሩም ከአካባቢ አካባቢ እንደየሁኔታው ይለያያል። ይሁንና በዓሉ ጎልቶ ከሚከበርባቸው አካባቢዎች መካከል ጉራጌ፣ ሲዳማ፣ወላይታ፣ እና አገው ምድርን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። ይህ ጽሑፍ በተለይም በአገው ምድር ያለውን ደማቅ አከባበር እና ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የደን ጭፍጨፋ ለመግታት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
የበዓሉ ዝግጅት እና የዋዜማ (መስከረም 16) ሥነ-ሥርዓት
በአገው ምድር የመስቀል በዓል ዝግጅት ከነሀሴ ወር ጀምሮ ይካሄዳል። ለበዓሉ ድምቀት ሲባል የተለያዩ የዛፍ ዓይነቶች (እንደ ሰሳ፣ ብሳና፣ ብርብራ፣ ውልክፋ እና የመሳሰሉት) ተቆርጠው ይዘጋጃሉ።
መስከረም 16 ቀን፣ ሁሉም ሰው በየራሱ የሰብል አዝመራ መሀል ላይ "ሰብሉን አለምልመው፤ አረሙን አጥፋው" በማለት የተዘጋጀውን ቀጠን ያለና ቅርፊቱ የተላጠ ነጭ እንጨት ይተክላል። በዋዜማው አመሻሹ ላይ የተቆረጠው የዛፍ ግንድ ቅርፊቱ ተልጦ ነጭ ይሆንና የሠፈሩ ሰዎች በየቤቱ እየተጠራሩ 'ግንድ የማስገባት' ሥነ-ሥርዓት ያከናውናሉ። ይህ ሥነ-ሥርዓት በዕድሜ አንጋፋ ከሆነው ቤተሰብ ተጀምሮ በየቤቱ በወረፋ ይቀጥላል።
ግንድ ለማስገባት በየቤቱ ባህላዊ አረቄ፣ ጠላ፣ አብዚ (አነባብሮ፣ ቅቤ በአዋዜ፣ አይብ፣ ሽሮ ወዘተ)፣ ለምለም ሣር እና ቡና ይዘጋጃል። አንጋፋው ቤት ግንዱ ሲገባ የተዘጋጀው ምግብና መጠጥ ይቀርባል፤ በዚሁ አጋጣሚ ስለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውይይት ይደረጋል። ግንዱ ወደ ቤት ገብቶ በእሳት ከተያያዘ በኋላ፣ እሸት በቆሎ ሽፋኑ ሳይወገድ ይጠበሳል፤ ሲበስልም ይበላል።
የበዓሉ ዕለት (መስከረም 17) አከባበር
መስከረም 17 ማለዳ፣ የተዘጋጀው ጭቦ ይበራና "ድሩፃ" እየተባለ ቤቱ፣ ማብሰያ ቤቱ፣ የጥጆች ቤት ወዘተ አንድ ጊዜ በበራው ጭቦ ወጋ እየተደረገ ይዳረሳል። በመቀጠልም በየቤቱ በዋዜማው የተደመረው ደመራ በተያያዘው ጭቦ ይለኮሳል።
ቀጥሎም የሰፈሩ ሰው በሙሉ ትልቁም ትንሹም እንደየአቅሙ ነጭ አዳዲስ ልብስ በመልበስ "እዮሄ" እየተባለ በጋራ ወደ ተዘጋጀው የጋራ ደመራ ያመራል። በባህሉ መሰረት ሴቶች ወደ ደመራ ቦታ ጭቦ ይዘው አይሄዱም። አብዛኛው የሰፈር ነዋሪ መሰባሰቡ ሲረጋገጥ፣ በሽማግሌ እና በካህን ምርቃት ተደርጎ "ድሩፃ" እየተባለ ደመራው ይለኮሳል።
የተለኮሰው ደመራ ነዶ እስኪያልቅ እና መሀል ላይ እንደ ምሰሶ የቆሙት አቋሞች እስኪወድቁ ይጠበቃል። የአቋሙ አወዳደቅ የራሱ የሆነ ትርጉም አለው፤ ወደ ምስራቅ ከወደቀ "ዘመኑ የተባረከ፣ አዝመራውም ምርት የሚታፈስበት ዘመን ነው" ተብሎ በባህል ይታመናል። ደመራው ነዶ ካለቀ በኋላ ከየቤቱ የመጣው መብል እና መጠጥ ይቀርባል። ቀኑ የፍስክ ቀን ከሆነ በእለቱ የእርድ ሥነ-ሥርዓት ተከናውኖ ውሎው እዚያው ደመራ ቦታ ይሆናል።
ማሳሰቢያ፡-ተከታዮቻችን የበዓሉን አከባበር ለማስታወስ እንጂ በትክክል ተገልጸል ለማለት ስላልሆነ እንድትረዱልን እንፈልጋለን፡፡
የደን ጥበቃ መልዕክት እና ጥንቃቄ
ይህ ሁሉ ሲደረግ የበዓሉ አከባበር በአብዛኛው ከደን ውጤቶች ጋር የተያያዘ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ ለአገር በቀል ዛፎች መመናመን የራሱን የጎላ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል። ስለሆነም በዓሉን ስናከብር ለተፈጥሮ ደኖች ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። የሚከተሉትን ነጥቦች ተግባራዊ እንድናደርግ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡-
• የደን ውጤቶችን ብዙ ከመጠቀም ይልቅ በጥቂቱ እንጠቀም። ስንጠቀምም ከስሩ ከመቁረጥ ይልቅ መልሰው ሊያቀጠቅጡ የሚችሉ የዛፍ ዝርያዎችን ቅርንጫፎች ብቻ እንቁረጥ።
• ትኩረታችንን በጥንቃቄ እና በሰው ሰራሽ ዛፎች ላይ ማድረግ ይጠበቅብናል።
• ከተፈጥሮ ደኖች ውስጥ የደን ውጤቶችን መቁረጥ ፍጹም የተከለከለ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል።
• ይህን በዓል እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በደኖች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ግለሰቦች ካሉ ህብረተሰቡ ሊከላከላቸው ይገባል። ምክር የማይሰሙ ካሉም ለህግ አካላት ጥቆማ መስጠት አስፈላጊ ነው።
መልካም የመስቀል በዓል እንዲሆንላችሁ ከወዲሁ እንመኛለን!
18/09/2026
17/09/2026
16/09/2026
መስከረም 06/2019 ዓ.ም
እንጅባራ፣
የ2019 በጀት ዓመት የሁለት ወራት የተግባራት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በስኬት ተካሄደ
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ከዞኑ ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በመሆን የሁለት ወራት የተግባራት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ አከናውኗል።
የውይይቱ እና የግምገማው ዋና ዋና ነጥቦ
በ2018 በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ላይ ከባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር በመሆን የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸም የተገመገመ ሲሆን፣ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መካሄዱ ይታወሳል። በመሆኑም ለ2019 በጀት ዓመት የሚያገለግል የተቀናጀ ዕቅድ እና መደበኛ የሪፖርት ፎርማት ወደ ሁሉም ወረዳዎች መላክ ተችሏል።
የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ የሁለት ወራት ተግባራት አፈጻጸም ከወረዳ ኃላፊዎች እና ከከተማ አስተዳደር ተወካዮች ጋር በመሆን በጥልቀት ተገምግሟል።
በዞኑ የአካባቢና ማህበረሰብ ተጽዕኖ ግምገማ ቡድን መሪ በኩል በተለያዩ መሠረታዊ የሥራ ዘርፎች ላይ የተከናወኑ ተግባራት በጥንካሬ እና በክፍተት ተለይተው የቀረቡ ሲሆን የቀረቡት የግምገማ ነጥቦችም፦
1. በአካባቢና ማህበረሰብ ተጽዕኖ ግምገማ
2. በአካባቢ ኦዲት (Environmental Audit)
3. በደን ዘርፍ ልማትና ጥበቃ
4. በአካባቢ ትምህርት እና ግንዛቤ ማስፋፊያ
5. በብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ተግባራት ናቸው፡፡
ውይይት እና የቀረቡ አስተያየቶች:-
በቀረበው አጠቃላይ ሪፖርት መሠረት የተሳተፉ የወረዳ ኃላፊዎች እና የከተማ አስተዳደር ተወካዮች በየዘርፉ ያጋጠሟቸውን ሁኔታዎች፣ የታዩ ጥንካሬዎችን እና ክፍተቶችን በመዳሰስ በስፋት ውይይት አድርገውበታል።
የቀረቡ ቀጣይ አቅጣጫዎች:-
የመድረኩን ማጠቃለያ የሰጡት የተጠሪ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ የሚከተሉትን ዋና ዋና መመሪያዎች አስተላልፈዋል፦
• በጥንካሬ የተነሱ በጎ ተግባራት ይበልጥ ተጠናክረው እና ተስፋፍተው እንዲቀጥሉ፤
• በድክመትና በክፍተት የተለዩ ነጥቦች በቀጣይ የሥራ ወቅት ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲታረሙ፤
• በቀጣይ በሚደረጉ የተግባራት አፈጻጸም ግምገማዎች ላይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉም አካላት በርብርብ እንዲሰሩ በማሳሰብ ስብሰባው በተቀመጡት አቅጣጫዎች ላይ ሙሉ ስምምነት በመድረስ በስኬት ተጠናቋል።
14/09/2026
በተቋማት መካከል ጠንካራ ትብብር መፍጠር ዘላቂና አወንታዊ ውጤት ያመጣል።
መስከረም 01/2019 ዓ፣ም
መልካም የአዲስ ዓመት እና የእንቁጣጣሽ በዓል ይሁንልዎ!
ነገ እርድ ይከናወናል ስለሆነም በዓላትን ስናከብር ደስታችንን ሙሉ የሚያደርገው የአካባቢያችን ጽዳትና ጤንነታችን ሲጠበቅ ነው!
ለበዓል ከምናደርገው የእርድ ሥነ-ሥርዓት ጋር ተያይዞ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች ባልተጠናከሩባቸው ቦታዎች የሚፈጠሩ የእርድ ተረፈ-ምርቶች ለአካባቢያችን ብክለት ዋነኛ መንስኤ እየሆኑ ይገኛሉ።
⚠️ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው ጎጂ ድርጊቶች፡
የእርድ ተረፈ-ምርቶችን (ደም፣ ሆድ ዕቃ፣ አጥንትና ቆዳ)፡
በወንዞችና በውሃ አካላት፣ በመንገድ ዳር፣ በዲችና ቦዮች፣ አጥርን በማስጠጋት ወይም በሰዋራ ቦታዎች ላይ መጣልና ማስወገድ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል።
እነዚህ ባልተገባ መንገድ የሚወገዱ የእርድ ተረፈ ምርቶች የሚያስከትሏቸው አደጋዎች፡
• የውሃ እና የአየር ብክለት፡ ወንዞችንና የመጠጥ ውሃን ይበክላል፤ ደስ የማይል ጠረን ይፈጥራል።
• የጤና ስጋት፡ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች መንስኤ የሆኑ ነፍሳትንና በሽታ አምጪ ህዋሳትን ይስባል።
• የከተማ ገጽታ፡ የአካባቢያችንን የተፈጥሮና የከተማ ውበት ያበላሻል።
ጥሪያችን፡
የበዓሉ ደስታችን በበሽታና በብክለት እንዳይደበዝዝ፡
1. የእርድ ተረፈ-ምርቶችን በጥልቀት በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ በመቅበርና በደቃቅ አፈር በመሸፈን፣
2. የተዘጋጁ የቆሻሻ ማከማቻዎችን በአግባቡ በመጠቀም፣ አካባቢያችንን ከብክለት እንታደግ!
"የጸዳ አካባቢ - ለጤናማና ደስተኛ አዲስ ዓመት!"
አካባቢያችንን በጥንቃቄ እንጠብቅ!
መልካም አዲስ ዓመት! 🌼 በዓላችንን በጽዳት፡ አዲሱን ዓመት በጤና እንቀበል!
10/09/2026
ጳጉሜ 5/2018 ዓ.ም
ለፌስቡክ ተከታዮቼ በሙሉ
እንኳን አደረሳችሁ!
እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ በሰላም አሸጋገረን።
አዲሱ 2019 ዓ.ም የሰላም፣ የመቻቻል፣ የፍሰሀ፣ የአንድነትና የመተሳሰብ ዘመን ይሁንልን!
አዲሱ ዓመት፡- ይቅር ተባብለን ሰላም የሚሰፍንበት፣ ከቦታ ቦታ በሰላም የምንቀሳቀስበት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሚፈቱበት፣ ታርሶ የሚታፈስበት፣ተነግዶ የሚተረፍበት፣ በትምህርት ዕውቀት የሚገኝበት ሰርተን የምንበለፅግበት
በአጠቃላይ ፍቅርና ደስታ የተሞላበት ዓመት ያድርግልን!
መልካም አዲስ ዓመት! እንቁጣጣሽ!
Category
Contact the organization
Website
Address
Amhara Region
Injibara